ፖሊሶቹ ፊት ምስኪኗ ሴትዬ ላይ 18 ጥይቶች አፈሰሰባት

ፖሊሶቹ ፊት ምስኪኗ ሴትዬ ላይ 18 ጥይቶች አፈሰሰባት

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከተሰሙት አስደንጋጭ ዜናዎች መካከል አንዱ ነው፣ ሴትየዋ ላይ የዘነበው የተኩስ እሩምታ፡፡ እንደእማኞች ቃል ከሆነ ሴትየዋ እናቷን ይዛ በመኪናዋ ገዳይዋን ለማምለጥ እየበረረች ነበር፡፡ መንገዷ ላይ የገጠማትን ማንኛውንም ፖሊስ ከመልአከ ሞት እንዲያስጥላት ለመጠየቅ ነበር የምትበረው፡፡

ቢሆንም መንገዱ ሁሉ እንኳን የጥበቃ ፖሊስ ቀርቶ የትራፊክ ፖሊስም አይታይበትም፡፡ ምናልባት የፖሊስ አባላት ሁሉ ከጸሐይዋ ለመጠለል ጥላ ሥር ሸሸግ ብለው ተቀምጠው ይሆን? … በዚያ ላይ መንገዱ በተሸከርካሪ እጅግ ተጨናንቆ ስለነበር ከኋላዋ የሚከተላትን ሞት ለማምለጥ የሚያስችላት አልነበረም፡፡ የምትችለውን ሁሉ ተጣጥራ ሁለት ጎስቋላ ፖሊሶች ጋር ደረሰች አሉን እማኞች፡፡ ልክ በዛው ሰዓት ታዲያ ሞት ከኋላዋ እኩል ደረሰ፡፡

ምስኪኗ ሴትዬ ላይ 18 ጥይቶች አፈሰሰባት፤ በአደባባይ!! ፖሊሶቹ ፊት!! ከ18 ጥይቶች ውስጥ የተወሰኑትን እንኳ ለማስቀረት አልቻሉም በአካባቢው የነበሩት ሕግ አስከባሪዎች፡፡ ቀጥሎ ገዳይ ወደሟቿ እናት ተጠግቶ በአንዲት ጥይት “ብቻ” መትቶ ጣላቸው፡፡ ሌሎች ሁለት ሰዎችንም በጥይት አቆሰለ፡፡ ፖሊሶቹ እናቲቱን እንኳ ማስጣል አልቻሉም፡፡ ምናልባት ከጥይቱ ዝናብ ለመጠለል ጥላ ሥር ሸሸግ ብለው ይሆን?

ግዳይ የጣለ የመሰለው ነብሰ ገዳይ ባዶ መሣሪያውን ጥሎ እንዲህ በማለት እጁን ለአካባቢው ሰዎች ሰጠ፡፡ “የገደልኩት ሚስቴንና እናቷን ነው፤ ልጆቼን እንዳላይ ከልክለውኛል፡፡ ሞት ይገባቸዋል፡፡”አዎ! ሕግጋት እንጂ ሕግ አስከባሪ በሌለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀለኞች ፈራጅ ቢሆኑ አይገርምም፡፡ ተራው ወንጀለኛ ቀርቶ ቱባዎቹ ወንጀለኛ ባለሥልጣናትስ እስኪፈረድባቸው ይፈርዱ የለ!?
ዱዲ ፍቅር

Leave a comment